Home Events IEWO Radio & ArchiveArticles & Papers Press Release Poems Become a Member

ምጽአት

By: cosmos-2000, June 2009

ካገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ...መባሉን እያወቀች

ያልፍልኛል ብላ ሕፃን ልጇን አቅፋ ስደትን መረጠች::

መከራ በዝቶባት መምረጥ ተገደደች ካለመኖር መኖር

ከሰው ላይ ሰው ጭነው በታንኳ ታጭቃ ወደ ውጭ ስትበር

ሜዲትራንያን ግብር አስከፈለ ቀንቶ በቀይ ባሕር::

ወያኔን ቢጠሉ ሄዱ ወደ ስደት ውሃው ይብላን ብለው

ከሞት እየሸሹ ወደሞት ይጓዟል ይሏችኋል ይህ ነው::

 

ወጣት አበቦችም በጠራራው ፀሐይ ተሽጠው ሲሄዱ

እንደ ሰው ሰው መሆን አቃታቸውና ስንቶች ተዋረዱ::

ወተሽ እንዳትጠፊ አቤት እንዳትይም በሩን ቆልፎብሽ

ምግብ አዘጋጅተሽ ደክሟታል ሳትባይ ዕቃውን አጣጥበሽ

ወጥቶ ለመጫወት ከጓደኞችሽ ጋር እረፍት የት አግኝተሽ::

የባርነት ኑሮ እንድትኖሪ አውቃለሁ የቁም ስቃይ አይተሽ

ለማይቀረው ሞቱ መገላገል ፈለግሽ ሕይወትሽን አጥፍተሽ::

ተቆርቋሪ ቢያጡ በአራቱ ማዕዘናት ሄዱ ተሰወሩ

በየደረሱበት ምግባረ ብልሹ ተብለው ተጠሩ::

ለነፃነት ሞተው ተተኪውን ትውልድ እንዳላስከበሩ

ልጅማ አላወጡም ተወልዶም ይሆናል ይታያል ተግባሩ::

እንኳን ለራሳቸው ለአፍሪካ ነፃነት ለትግል ቀስቅሰው

ታሪካቸውማ በዓለም ተመዝግቧል አንድም ሰው አይክደው::

ለጥቁሮች ማጎሪያ ቅኝ ገዢዎቹ እስርቤት ሲሠሩ

ቅኝ ገዢው ሳይገባ ኢትዮጵያውያኑ እየገቡ ታጎሩ

እንዳርበኞች ቢሆን ይታያቸው ነበር ዱሩ ሸንተረሩ::

 

በርከት ያሉ ናቸው የነፃነት ትግልን በጧት የጀመሩ

ማቸነፍ ማለትን ሳያውቁ ተጉዞው በውር በድንብሩ

ሃቅን ስለያዝን ለማቸነፍ በቃን የሚሉት ዲስኩሩ

ጩኸትማ ሰማን የወያኔዎችን ሃሰት ሲናገሩ::

ሃቅማ ቢይዙ ፀሃይ እየወጣች ብርሃን እናይ ነበር

አንደበት ተዘግቶ ታስረን ተባረርን በራሳችን አገር

ዘረኛና አጃቢው ሲሆኑ አየናቸው ምሰሶና ማገር::

 

ላንድነት የሚቆም በመስዋዕትነቱ አቅርቦና ስቦ

መታመን በተግባር መታፈር በከንፈር ብሎ ተረባርቦ

በሃቅ እየዘገቡ ለጋራ ጥቅማችን ሥራውን መዝግቦ

ከወረደው ጥበብ “አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ስቦ”

ልቦና ለሰጥው ፍንትው ይልለታል ከፊታቸው ቀርቦ::

ሹክ ብላቸውም መልስ አልሰጠኝ አሉ በዝቶ ውዥንብሩ

በማኝ ፊት ብናገር ብናርፍ ይሻለናል ብለው ተሰወሩ

ፈርተን ነው ካላሉ እኛ የማይገባን ምንድን ነው ሚስጥሩ?

እናብር ስንለው እኔ ተቀብሬ መገኘቱን ይሻል ካዘኑ ከቀብሩ

ዝምታ ወርቅ ነው መባል ይቁም በቃ በርትቷል ችግሩ::

 

በሰከሩ ቁጥር ሚገድሉን ከሆነ እስቲ ምቱ መላ

ዓይናፋር ይመስል ዝምታን ስትመርጡ ሕዝቡ እየተቆላ

ሂዱ ተተፍተፉ እንዲወጣላችሁ የሰው ዓይነ ጥላ::

ስልቱ ገድሎ ማዳን ግንባር ቀደም ሆኖ ካሳየን አጉልቶ

አነጣጥረህ ምታ ደግ ነህ አልተባልክ አድሮና ሰንብቶ::

የሚጽፍም ይጻፍ ሸንጎ ፍጠሩና እስቲ ተማከሩ

አትሸፋፍኑት ይታወቅ ሰው-በላው ሰይጣናዊ ምክሩ::

 

ዝምታ ወርቅ ሚሆን:- ተስፋ ሲደርቅ ነው ወይስ ሲለመልም?

ተስፋማ ይለመልም ነጣጣይ ዘረኛ ካገር እንዲል እልም::

ተስፋንማ ሥሩ ጥቂት በጥቂቱ እኛም ደጀን ሆነን

ዕውን የሚሆነው ግፈኛ ተመቶ አገሩ አገር ሲሆን::

ምኞታችንን ገድሎ ስጋችን ጨረሰው እየዋለ እያደረ

አለመያዝ ደጉ አለመቀደም የተያዘው ሁሉ እንደወጣ ቀረ::

የጸሃፊን ብዕር በጉልበት አባሮ ሃሳብ እየቀበረ

ጅሉም ስላልገባው ግፈኛውን አምኖ ሕይወቱን ገበረ::

ያውም በኛው አገር አሠሩን ገሰሱን እሥረኛ ይበላል

የሚቀምሰው አጥቶ ሕዝቡ በየተራ በረሃብ ክልትው ይላል

የሕዝባችንን ኑሮ ዓይናችን ዓይቶታል ልቦናችን ያውቃል

እንዲያው የለየለት ቁርጡ የታወቀው የእሥረኛው ይሻላል::

ትምህርት ቤት ገባሁ ገጠሩንም አየሁ ዙሬ ተዟዙሬ

አብሮ መኖር ተማርኩ ትዳርን መስርቼ ሥራም ተቀጥሬ

ውቅያኖስ አየሁኝ ባሕር አቋርጨ ውጭ አገርም ኖሬ

አገር በማጥፋቱ ወያኔን የሚያስንቅ አጣሁኝ መርምሬ::

 

ነግደው:- ለምነው:- በተገኘው ገንዘብ አጋዚን ተመቸው

በገደሉ ቁጥር ብሶባቸው መጡ ደም እየጠማቸው

የወገናችን ደም መጠጣት ሲበዛ ስካሩ አዞራቸው::

ለማምነው ሲያመጡ በገንዘቡ ብዛት ጎረቤት ወረሩ

አማራም አልቀረ ኦሮሞ ሶማሌ አኝዋክና አፋሩ

ሲዳማና ትግሬው የከታማው ነዋሪ እንዲሁም ገጠሩ

በእብሪት ተወጥረው ማን አለብኝ ብለው አገር መነጠሩ::

 

ከሃዲና ባንዳ አገር አከሰረ ባንኩንም ዘረፈ

ሚቆረቆር መስሎ የልቡን እየሠራ ፍትሕ አዛነፈ::

ታሪክን ሰርዞ ለሰንደቃላማው የግል ትርጉም ሰጥቶ

በመዝሙር ሲያጅቡ ጆሯችንን ደፈንን ጩኸቱ በርትቶ

ቢውለበለብ ቅሉ በልብ አናቅፈውም የኛን ትርጉም ትቶ::

 

እራሱ አጽድቆ እራሱ ከልክሎ መብትን አፈነና

አየር ደመናውን ሰማዩን ለማየት ቀና በሉ አለና

ካለእኔ በስተቀር ከአናታችሁ በላይ ከቶ ማን ቆመና

ዝናቡም የኔ ነው ውሃ የቋጠረን ማንሳፍፍ ደመና::

በነጎድጓድ ድምጤ ፍጡራንን ሁሉ ማኖር አሸብሬ

መብረቁን ሳባርቅ ስሃሊለነ ብለው ይስገዱ ወደ እግሬ

ከዋክብትን እዩ የዘራኋቸውን ወጥሬ ገትሬ

ጨረቃንም ሰጠሁ ማማረራችሁን ስለሰማሁ ወሬ::

የሁሉም ማዕከል ፀሓይማ እኔ ነኝ እምቦለሌ ማዞር

ምንም ሳላዛንፍ ጨለማና ብርሃን ወቅቱን ማቀያይር

ሙቀት እየሰጠሁ እፅዋት ለምልመው ሚበላ የምቸር::

 

ይህን ሁሉ አድርጌ ሊፈትነኝ መጣ ጉልበቴ ተንቆ

አቅሜን ላስመሰክር ከአፋር በሚነሳው የሽምጥ ሸለቆ

አለቱን ብረቱን አንድ ላይ አቅልጨ ገድል ልሥራ ብዬ

እንደ ማንዳ ሃራሮ እሳተ ጎመራ ወደላይ ገንፍዬ

እንደ ዳላፊላ የእሳት አለሎውን አውጥቼ አንቀልቅዬ

ምድርን ያለምሰሶ ሰማይን ያለ ባላ ቀጥ አርጌ አቁሜ

ጉልበቴን ፈርታችሁ እንድትሰግዱልኝ ነው ይህ ሁሉ ድካሜ::

ልባችሁ ሸፍቶ ጌታ ሆይ ብላችሁ መች እኔን ጠራችሁ?

ከእኔ በላይ ላሳር ክብሬን አትጋፉ አሁንስ ገባችሁ?

ቁጣዬ በርትቶ ደጋግሜ ሞከርኩ ክንዴን ላሳያችሁ::

ለምድራዊ ስልጣን ቀናዒ መሆኔን ያዳም ዘር እንዲያውቅ

ዕድሜዬ ሚረዝመው በእኔ ሥር ሲውል ነው ያገሪቱ ወርቅ::

ሁለቱን እሴቶች ከመዳፌ አውጥቶ የሚወስድ ከመጣ

የጦር ሠራዊቴ እርምጃ ይወስዳል የለብኝም ጣጣ::

ቢረገም ነው እንጂ ሰይጣን መልአክ ነበር ብለው ያስተማሩኝ

ዕውነት እንደሆነ በሕይወት እያለሁ ይኸው ተረዳሁኝ::

አላቂነታችው አልታይ ብሏቸው በትዕቢት ቀጠሉ ግፉን ሰቆቃውን

እንዴት ቢንቁን ነው?.…እየጠሉ ገዙን ደንቆሮ አድርገውን::

ፈጣሪን በማመን በደም ባጥንታቸው ወያኔን ሊያባሩ

ያልሰማህ ከሆነ ከተነሱ ባጁ ሃሞተ ኮስታሮች የማይበገሩ::

ጥቂቶች ቢሆኑም ሕዝባቸውን አምነው ፈተናውን አልፈው

ሳይንበረከኩ ጥርት ባለ ራዕይ ባላማ ታጅበው

ከፈጣሪ ታዟል የነፃነት ቀንዲል ሊያበሩ ከፍ አርገው::

 

እንደ እግዚአብሔርም ሕያው ነኝ ሁሉን አደርጋለሁ

ሕዝብ እንዲገዛልኝ የፈጣሪ ጥበብ ይኸው ይዣታለሁ

እያለ ቀባጥሮ እምብዛም አይቆይም እንደ ጉም ይበናል

በእርሱ መቃብዕር ላይ ጥበብም ጉልበትም የሕዝቡ ይሆናል::

መኖር መደምሰስም በእኔ ፈቃድ ነው ሲል

መነሻውን ሳያውቅ የፈጣሪን ጥበብ የያዛት ሲመስል

ምንድነው ዝምታው ከሕዝብ ጋር ሆነን ዘግ ማድረግ ስንችል

ጤና የሚገኘው መዝምዘን ሰርስረን ገርስሰን ስንጥል::

IF
(From the "Miseducation of the Negro")


“If you can control
a man's Thinking
you do not have to worry
about his action.
When you determine
what a man shall think
you do not have to concern yourself,
about what he will do.If you make a man
feel that he is inferior,
you do not have to compel him
to accept an inferior status
for he will seek it himself.If you make a man think
that he is justly an outcast,
you do not have to order him
to the back door.
He will go without being told
and if there is no back door
his very nature will demand one."

Carter G. Woodson

Poem from Lemelm Tsegaw 

My Brother…

 What is wrong my brother?

Don’t you have a shelter?

Is your life the same as Monkeys whose roofs are the woods and the leaves? 

What is wrong my brother?

Don’t you have an answer?

What is wrong my brother?Is the barrel of a gun your only shelter?

What is wrong my brother?

Are you forever a rebel and a fighter? 

 

Lemlem Tsegaw, May 10, 2007

Dedicated to all African men who believe peace is possible only through the barrel of a gun

Letter from Ethiopian Women living in SouthAfrica

10/10/2006

                                     ከደቡብ አፍሪካ     

                           እልል ብለናል                  ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት  መመስረቱን የሚያበሥር ዜና ደብተራው በሚባለው ድሕረ ገጽ ላይ ስንመለከት የተሰማን ደስታ ልክ አልነበረውም ።  እኛ ስማችን ሃና ከበደ፣ ሳራ ሰለሞንና  ዘውዲቱ መንገሻ የተባልን ሴቶች ሶስታችንም የምንኖረው በደቡብ አፍሪካ ሲሆን ቀደም ብሎ በሳውዲ አረቢያ ሪያድ ውስጥ  ስንኖር ቆይተን በዓመታችን ከሳውዲ አረቢያ ተጠርፈን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰን ነበር።  መጀመሪያውኑም ከሃገራችን ተሰደን ወደ አረብ አገር የሄድነው በሃገራችን ውስጥ የተረጋጋና በሰላም የመኖር ተስፋው ሲጨልምብንና ሰርቶ የመብላት እድሉ ሲጠብብን አንዳዶቻችን ልጅ እናሳድግ ብለን፣ አንዳዶቻችን ደግሞ ደካማ ወላጆቻችንን ልንረዳ ያስችለን ይሆናል ከሚል በመቸገር ነው።  ሆኖም ግን እድላችን ሆኖ በሳውዲያ አረቢያ ተደብቀን እንኖርበት የነበረበት ቦታ ተይዘን ከተመልስን በኋላ እንደገና ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሄድ ያንኑ የተሰደድንበትን ችግራችንን ለመወጣትና ሰርተን ለመብላት ብለን  እዚህ እንኖራለን።  ይህንን የሴቶች ድርጅት የመመስረቱን ዜና አይተው የነገሩን ጓደኞቻችንን(ኢትዮጵያዊያን አይደሉም)  ስንጠይቃቸው ያገኙበትን ድህረ ገጽ ሲያሳዩን በራሳችን ቋንቋ በአማርኛ ተጽፎ ተመለከትን።  ይበልጥ ተደሰትን።  ውድ እህቶቻችን ! በሀገራችን ውስጥ ባለው ያለመረጋጋት ሁኔታ ተገፍተን በስደት በሰው አገር ለዚያውም አፍሪቃ ውስጥ ስንኖር ለጊዜው የመጠለያ ያህልና እጆቻችንን ጠብቀው ለሚያድሩት ልጆቻችንና ወላጆቻችን ስንል እንደሆነ የምትረዱት ቢሆንም እንዲህ አይነት ያለመረጋጋት  በዓለም ላይ እስከአለ ድረስ በየትኛውም ቦታ ቢሆን የመጀመሪያው የችግሩ ሰለባዎችና ተጠቂዎች እኛና ልጆቻችን መሆናችንን ስናስብ ምን ያህል በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንድምንባዝን አመላካች ነው። በእንዲህ አይነት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መሬት ተደፍቶብን በምንኖርበት ሁኔታ ላይ ኢትያጵያዊ የሆነ ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት ተመሰረተ መባልን ስንሰማ ባይመቱበትም ያስፈራሩበታል እንድሚባለው በደቡብ አፍሪካ የምንኖረው እኛና ብዙ እህቶቻችን ሰለራሳችን ችግሮች የምንተነፍስበት ቤት ያገኘን ያህል ተመለክተነዋል።  እያንዳንዱ አንዳንድ ጡብ ካስቀመጠ ቤት ይሰራል ተብሏልና እባካችሁ የድርጅቱን አድራሻ አሳውቁንና እኛም በቤታችን አንዳንድ ነገሮች እንጨዋወት።  ድምጻችሁ አይጥፋ እንላችኋለን።                               ሃና ከበደ          ሳራ ሰለሞንና

           ዘውዲቱ መንገሻ ነን !

Home | | ©2007 IEWO